Skip to main content
Image
news1
ሀዋሳ፣ ሐምሌ26/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የሀዋሳ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በ2017 ዓ.ም ትምህርት ዘመን ለ26ኛ ዙር ከ1 ሺ 100 በላይ ተማሪዎችን በዛሬው እለት አስመርቋል፡፡ የኮሌጁ ዲን ዶ/ር ንጋቱ ቱአሻ እንደተናገሩት በዛሬዉ እለት በመደበኛ እና በሳምንት መጨረሻ መርሃ-ግብሮች በአዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ በ12+2 ዲፕሎማ፣ በቅድመ አንደኛ ትምህርት መስክ፣ በ12+1 ሰርቲፊኬት በመደበኛ መርሃግብር እንዲሁም በሳምንት መጨረሻ መርሃግብር በ4 ማዕከላት ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ በአጠቃላይ 1136 ተመራቂዎች መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ ከድህነት እና ኋላ ቀርነት ተላቃ ካደጉ ሀገሮች ተርታ ለመሰለፍ ትምህርት ዋነኛ መሳሪያ መሆኑ እሙን ነው ብለዋል፡፡ ይህንን በመገንዘብ በሀገር ደረጃ በትምህርት ዘርፍ የሚታዩ ጉድለቶችን በመፈተሽ ለቀጣይ ዓመታት የሚተገበር የትምህርት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ በተለያዩ ደረጃ በተከናወኑ ውይይቶች ዳብሮ በአሁኑ ጊዜ እየተተገበረ መሆኑን ዶ/ር ንጋቱ ጠቁመዋል፡፡ በፍኖተ ካርታውም ላይ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ የመምህራንን ጥራት ማሳደግ አስገዳጅ ሆኖ በመገኘቱ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ይገኛል ያሉት የኮሌጁ ዲን ከመቼውም ጊዜ በላይ በሁሉም መርሃግብሮች ለሚሰጡ ስልጠናዎች የጥራት ጉዳይ የማይደራደረው ቀዳሚ ጉዳዩ አድርጎ ተግቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡ የቅድመ አንደኛ ትምህርት ለልጆች ቀጣይ የትምህርት ምዕራፍ ሁነኛ መሠረት የሚጥሉበት ስለሆነ ከፍ ያለ ትኩረት ተሰጥቶበታል ብለዋል፡፡ ኮሌጁ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በምርምር ዘርፍም አበረታች ውጤቶችን እያስመዘገበ መጥቷል ብለው በዚህ አመት ብቻ ከ10 በላይ የምርምር ሥራዎች እውቅና ባላቸው አለም አቀፋዊ ጆርናሎች የኮሌጁን ስም ይዘው የታተሙ ሲሆን ባለፉት 4 አመታት ብቻ ከ50 ያላነሱ የምርምር ስራዎችን ማሳተም ተችሏል ብለዋል፡፡ የሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ እና የዕለቱ የክብር እንግዳ አቶ በየነ በራሳ ከለውጡ ወዲህ የትምህርት ስብራቶችን በመለየት ረዥም መንገድ በመጓዝ ፖሊሲ ቀርፆ ትምህርት ከችግር ወጥቶ ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት ዜጎች እንዲያገኙ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ እንዳለ ገልፀዋል፡፡ ባለፉት ጊዜያት የካሪኩለም ስራ ተሰርቶ የትምህርት መሣሪያዎች እንዲሁም የስልጠና ማኑዋሎችና የተለያዩ ስራዎች በመስራት ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ ነው የገለፁትል፡፡ እንደክልል የትምህርት ችግሮችን በመለየት በተለይም በመሰረት ላይ መስራት ስለሚጠበቅብን ህፃናት በህፃንነታቸው የሚያስፈልጋቸውን ዕውቀት ለማስጨበት በቅድመ አንደኛ ላይ የተለየ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል ነው ያሉት፡፡ የክልሉ መንግስት ህዝቡን አሳትፎ የትምህርት ተሃድሶ ፕሮግራም ቀርፆ የቅድመ አንደኛ ትምህርት ትኩረት የተሰጠው ስለሆነ በርካታ ት/ት ቤቶችን ገንብቷል፡፡ ነባር ትምህርት ቤቶችን የማደስ ስራ በከፍተኛ ሁኔታ መሰራቱን ገልፀው ትምህርት ቤቶችን መገንባት ብቻ ሳይሆን ብቁ ተማሪዎችን ለማብቃት አስፈላጊ በመሆኑ ይህንን ሊያሳካ የሚችለው ብቁ ሃይል ያለው መምህር በመሆኑ መምህራንን በመደበኛውና በሣምንት መጨረሻው ቀን በማሰልጠን የሰለጠኑ መምህራንን ለማዳረስ በከፍተኛ ትኩረት እየተሰራ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡