Skip to main content
slide

የሀዋሳ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ አጭር ታሪክ

ወደግማሽ ክፍለዘመን የሚጠጋው የሀዋሳ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ታሪክ፣ የኮሌጁን ስኬት ያሳያል፡፡ የሀዋሳ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ (ሀመትኮ) የተመሰረተው በ1969 ዓ.ም. ነው፡፡ ይህ ዓመት በክልሉ አዲስ የትምህርት ተቋማት የተገነቡበት፣ በተለይም የመምህራን ትምህርት የተከፈተበት ነበር፡፡ የሀመትኮ ታሪክ ከኮሌጁ ጋር የተያያዙ ታሪካዊ ሁነቶችን መነሻ በማድረግ በሁለት ወቅቶች ሊከፈል ይችላል፡፡ ይህም፣ የመጀመሪያ ወቅት እና ሁለተኛ ወቅት በመባል ይከፈላል፡፡ የመጀመሪያው ወቅት፣ ከ1969 - 1989 ያለውን ጊዜ የሚመለከት ሲሆን፣ ከ1989 ዓ.ም. በኋላ እስካሁን ያለው ደግሞ ሁለተኛው ወቅት ነው፡፡

የሀዋሳ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ታሪክ፣ የሀዋሳ የመምህራን ትምህርት ተቋም ከተመሰረተበት ከ1969 ዓ.ም. የሚጀምር ነው፡፡ በእዚህ ወቅት ተቋሙ በዋናነት የአንደኛ ደረጃ መምህራንን የማሰልጠን ኃላፊነት ተሰጥቶት ነበር፡፡ ተቋሙ ይዞ የተነሳው መርሃ ግብር እጩ መምህራኑ በተመለመሉበት ቦታ ሄደው እንዲያስተምሩ ለማድረግ ነበር፡፡ በተጨማሪም ተቋሙ በስራ ላይ ስልጠና (በክረምት) መርሃ ግብር የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስራ መሪዎችን ያሰለጥን ነበር፡፡ ተቋሙ በ1969 ዓ.ም. አጋማሽ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ የሚሰሩና የመምህርነትን ስልጠና ሳይወስዱ እያስተማሩ ያሉ የድጎማ መምህራንን ተቀብሎ የአጭር ጊዜ የስራ ላይ ስልጠና ይሰጥም ነበር፡፡ የሀዋሳ መምህራን ትምህርት ተቋም ምስረታ በኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በ1969 ዓ.ም. ካጋጠመ ታሪካዊ ክስተት ጋር የተያያዘ ነበር፡፡ ይህ ዓመት የኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ የአንደኛ ደረጃ መምህራንን በሰርተፍኬት ማሰልጠን ያቆመበት ዓመት ነበር፡፡ በመሆኑም፣ በኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ይሰጥ የነበረው የሰርተፍኬት መርሃ ግብር ወደሀዋሳ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ (ቀድሞ ሀዋሳ መምህራን ትምህርት ተቋም ወደሚባለው) ተዘዋወረ፡፡ ይህ መርሃ ግብርም ተቋሙ ወደኮሌጅ እስካደገበት እስከ 1988 ዓ.ም. ድረስ ቀጥሏል፡፡ ወደኮሌጅነት እስካደገበት እስከ 1988 ዓ.ም. ድረስም ተቋሙ ከ18‚779 በላይ መምህራንን በሰርተፍኬት አስመርቋል፡፡

የሀዋሳ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በ1988 ዓ.ም. ክረምት በይፋ የስራ ላይ ሰልጣኞችን ተቀብሎ በማሰልጠን ስራውን ጀመረ፡፡ ከ1988 እስከ 1989 ዓ.ም. ባሉት ወራትም፣ በትምህርት ሚኒስቴር እውቅና ካገኙ ሰባት ኮሌጆች አንዱ ነበር፡፡ በወቅቱ የመጀመሪያዎቹ የመደበኛ መርሃ ግብር ተማሪዎች በትምህርት ሚኒስቴር ከኮሌጁ መጋቢ አካባቢዎች ተመልምለው በኮሌጁ በመመደባቸው ይህንን ያሳያል፡፡ በመጀመሪያው የክረምት የስራ ላይ ስልጠና ላይም ይኸው ነገር ተተግብሮ ነበር፡፡

የሀዋሳ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ፣ ወደኮሌጅነት ካደገበት ከ1988 ዓ.ም. በኋላ ከ68‚347 በላይ መምህራንን በመደበኛና በተከታታይ ትምህርት መርሃ ግብር በዲፕሎማ አስመርቋል፡፡ ከእነዚህ የዲፕሎማ ምሩቃን ውስጥ 50 ያህሉ የደቡብ ሱዳን ዜጎች ነበሩ፡፡ ኮሌጁ ሊኒየር፣ ክላስተር፣ ስፔሻሊስት (ጄኔራሊስት)፣ ቴሶ በሚባሉትና በ12+2 እና በ10+3  ውስጥ በተካተቱት የስልጠና መንገዶች ውስጥ አልፏል፡፡ ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበርም 434 ሰልጣኞችን በትምህርት እቅድ እና አስተዳደር በዲግሪ መርሃ ግብር በተሳካ መልኩ አሰልጥኗል፡፡ በ2010 ዓ.ም. ላይም ከቀድሞ የደቡብ ክልል መምህራን ትምህርት ኮሌጆች ጋር ተወዳድሮ በማሸነፍ የመምህራን ትምህርት የልህቀት ማዕከል ሆኖ ተመርጧል፡፡

የሀዋሳ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ከ2014 ዓ.ም. ጀምሮ በመጀመሪያ ዲግሪ መርሃ ግብር በ13 የተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ስልጠና እየሰጠ ይገኛል፡፡ ቀዳማይ የልጅነት እንክብካቤና ትምህርትንም ከዚሁ ዓመት ጀምሮ በ12+2 የዲፕሎማ መርሃ ግብር መስጠት ጀምሯል፡፡ ከ2015 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ በአራት ማዕከላት፣ ማለትም በሀዋሳ፣ በይርጋለም፣ በአለታ ወንዶ እና በበንሳ ማዕከላት በዲፕሎማ እና በዲግሪ መርሃ ግብር ስልጠና እየሰጠ ይገኛል፡፡ ኮሌጁ 210 የአካዳሚ፣ 173 የአስተዳደር በአጠቃላይ 383 ሰራተኞችን ይዞ ስራውን እያከናወነ ይገኛል፡፡