Skip to main content

slide 

የዲኑ መልዕክት

የሀዋሳ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ የተመሰረተው በ1969 ዓ.ም. ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ላለፉት 45 ዓመታት በልዩ ልዩ የስልጠና ዘዴዎች መምህራንንና የትምህርት ባለሙያዎችን ተገቢ ዕውቀትና ክህሎት እንዲያገኙ በማድረግ እያፈራ ይገኛል፡፡ እስካሁን በ12+1 ሰርተፍኬት መርሃ ግብር 18‚779 መምህራንን፣ በ12+2 እና በ12+3 በዲፕሎማ የመደበኛና የተከታታይ መርሃ ግብሮች ደግሞ 68‚347 መምህራንን እንዲሁም ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር 434 ተማሪዎችን በትምህርት እቅድና አስተዳደር መስክ በመጀመሪያ ዲግሪ መርሃ ግብር አስመርቋል፡፡ ኮሌጁ በሀገሪቱ ደረጃ አስተማማኝና ብቁ ተቋም በመሆን፣ የመምህራን ትምህርት ስልጠና የልህቀት ማዕከል ሆኖ ተመርጧል፡፡

ኮሌጁ በዓለም አቀፍና በአገር አቀፍ ትብብር የሚታወቅ ሲሆን ለምሳሌም KOICA (Korea International Cooperation Agency), (PIN) People in Need- from the Czech Republic እና UNESCOን ከመሳሰሉ አጋሮች ጋር የተለያዩ የፕሮጀክት ስራዎችን ሰርቷል፡፡ በተጨማሪም BESO, VESO, TDP, WORLD LEARNING PIN, GEQIP, UNESCO እና ከመሳሰሉት ድርጅቶች የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ አግኝቷል፡፡ በተጨማሪም፣ 1990ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ በጎ ፈቃደኛ የውጭ አገር ዜጎች በኮሌጁ ውስጥ በማስተማር ስራ ላይ ተሳትፈዋል። በአገር አቀፍ ደረጃም ከኢትዮጵያ ትምህርት ቤት ዝግጁነት ኢኒሼቲቭ (ESRI) ጋር በመተባበር ቀዳማይ የልጅነት እንክብካቤና ትምህርት ክፍልን በኮሌጁ ድጋፍ ከሚደረግላቸው የቅድመ አንደኛ ትምህርት ቤቶች ጋር በማቀናጀት የአቅም ግንባታ ፕሮጀክትን በማከናወን ላይ ይገኛል። በየጊዜው በተደረገው ያላሰለሰ ጥረትም፣ በአሁኑ ወቅት ኮሌጁ ከፍተኛ መጠን ያለው የሰው፣ የቁሳቁስና የአስተዳደር ሃብት በማዳበር ለሌሎች ኮሌጆች አርአያ ለመሆን ችሏል። 210 የአካዳሚክ እንዲሁም 173 የአስተዳደር በድምሩ ከ383 በላይ ሰራተኞቹንም በማስተባበርና በመምራት፣ ጥራት ያለው ትምህርት በመስጠት፣ ጥናትና ምርምር በማድረግ እና በማህበረሰብ አገልግሎት ተግባራት ላይ በመሳተፍ ተልዕኮውን ቁርጠኛነት እየተወጣ ነው።

ውድ ባለድርሻ አካላት፣ ያለን ሀብት የሚናቅ ባይሆንም ከፍተኛ ጥራት ያለው ትምህርት ለመስጠት፣ የምርምር ውጤቶችን ተግባራዊ ለማድረግና የማህበረሰብ አገልግሎቶችን ለማከናወን በቂ አይደለም። ኮሌጁ የሀብት ማዕከሎችን በማሳደግ፣ መደበኛ የተከታታይ ሙያ ማሻሻያ ስልጠናዎችን በመስጠት፣ በቴክኖሎጂ የተደገፉ የመማር ማስተማር ሁኔታዎችን በማመቻቸት፣ የመረጃ አስተዳደር ቴክኖሎጂዎችን በማሻሻል፣ በቴክኖሎጂ የበለፀጉ የመማሪያ ክፍሎችን በማደራጀት፣ የሳይበር ደህንነትን በማሳደግና የተሻለ የተማሪና የሰራተኛ አገልግሎትን በመስጠት፣ ደረጃውን የጠበቀ የመምህራን ትምህርት የልህቀት ማዕከል ሆኖ ለመቀጠል አልሞ እየሰራ ይገኛል። በትምህርት ላይ የሚሰሩ ሀገር በቀልም ሆኑ ዓለማቀፋዊ አጋሮች፣ በሀገራችን ብሎም በአህጉራችንና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ጥራቱን የጠበቀ የመምህራን ማሰልጠኛ ተቋም ለመገንባት ከኮሌጃችን ጋር ትብብር እንዲፈጥሩ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡

በመጨረሻም የሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ትምህርት ቢሮ፣ ፋይናንስ ቢሮ፣ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን እና ሌሎች የክልል እና የሀገር አቀፍ ባለድርሻ አካላት ላደረጉት ድጋፍ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። በተጨማሪም አስተዋፅዖዋቸው በዋጋ ሊተመን የማይችለው የቀድሞ እና የአሁን የአካዳሚክ እና የአስተዳደር ሰራተኞች ምስጋና አቀርባለሁ፡፡ አብረን መስራታችንን እንቀጥልእጅ ለእጅ ተያይዘን እንደግ። አመሰግናለሁ! 

ንጋቱ ቱአሻ ፊሳ (ዶ/ር)

ተጠባባቂ ዲን

ኢሜል፡- ntuasha@gmail.com

ሞባይል ስልክ፡- +251-911-76-47-02